Facebook
ለዓለማቀፍ ረድዔት ድርጅቶች የቀረበ የሰብዓዊ
ዕርዳታ ድጋፍ ጥሪ
ከቴዎድሮስ ብርጌድ እና ከሰሜን አማራ ፋኖ
***
የአማራ ሕዝብ የገጠመውን የህልውና አደጋ
የመቀልበስ ተልዕኮ ይዞ ወደትግል ሜዳ የገባው ፋኖ የወጣበትን ሕዝብ ሰብዓዊ ሁኔታና ደህንነት
የመከታተል ብሎም የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት
ያምናል። ፋኖ የአማራ ሕዝብ የገጠመውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ የማይተካ ሕይወቱን እየገበረ ለነፃነት፣ ለፍትሕና እኩልነት በመፋለም ላይ ይገኛል።
በቀዳሚነት የሚታገልለት የአማራ ሕዝብም
በየአካባቢው ራሱን እንዲከላከልና የህልውና አደጋ
ምንጭ የሆነውን የብልጽግና አገዛዝ ሰራዊትን በደፈጣ እረፍት እንዲነሳ የትግል ስትራቴጂ እየሰጠ ያነቃቃል ያስተባብራል። በዚህም ከራሱ ከሕዝቡ የወጣው ፋኖ፣ የሕዝብ ትግል መሪነቱን በተግባር በማሳየት ላይ ነው።
በዚህ የተናበበ ትግል ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገባው የብልጽግና አገዛዝ ሕዝባችንን በፖሊሲ ደረጃ
በመቅጣት ላይ ይገኛል። አገዛዙ በሕዝባችን ላይ
የከፈተው ጥቃት መልከ ብዙ ሆኖ ዋተኛው ጥቃቱ ግን ረሃብን እንደጦር መሳሪያ በመጠቀም የትግል ማሸነፊያ መንገድ ለማድረግ በማሰብ የጀመረው ሰብዓዊ እርዳታን የመንፈግ ጅምላ ጨራሽ ውሳኔው ነው።
ፋኖ በስፋት ከማንቀሳቀስባቸው ቀጠናዎች አንዱ
የሆነው የሰሜን አማራ አካባቢ፣ በሰሜን ጎንደር ዞን
ከሚገኙ 11 ወረዳዎች ውስጥ ዘጠኙ በከፊልና ሙሉ
በሙሉ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፤
ከእነዚህ ውስጥ በሁለት ወረዳዎች ማለትም ጃናሞራ
እና በየዳ ግልፅ ረሃብ ተከስቷል። በተለይም ጃናሞራ
13ቱም የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ከፍተኛ ረሃብ
ተከስቷል። ምዕራብ እና ምሥራቅ ጠለምት
ወረዳዎችም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
የፋኖ ስትራቴጂ ጥናት ክፍል ከሲቪል አካላት ጋር
በመሆን ባሰባሰበው መረጃ መሰረት ድርቁ ወደረሃብ
ማደጉን ተከትሎ እስካሁን ከ120-135 የሚገመቱ
ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ አብዛኞቹ ሟቾች ወላድ
እናቶችና ህፃናት ናቸው። በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር
ዞን ብቻ ከ10,500 በላይ የዳልጋ እና የጋማ ከብቶች
በድርቁ ምክንያት ሙተዋል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ብቻ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች የዕለት ምግብ ረድዔት ጠባቂዎች ለመሆን ተገደዋል። ከእነዚህም ውስጥ 4000 ሺህ የሚሆኑት አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በሕይወት እና በሞት መካከል የመጨረሻው እስትንፋስ ላይ የሚገኙ ግፉዓን ናቸው።
ከድርቁ ጋር በተያያዘ እንደ ኮሌራ እና አተት ያሉ
ወረርሽኞች ተከስተዋል። በመንግሥት አቅም መቅረብ ይችሉ የነበሩ የወረርሽኝ መከላከያ መድኃኒቶች እና የሕክምና አቅርቦቶች ሆን ተብሎ እንዳይቀርቡ በመደረጉ ሕዝባችን በረሃብና በወረርሽኝ እንዲሞት በመደረግ ላይ ነው።
አገዛዙ ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ "ችግሩ ከአቅም
በላይ ሆኗል" የሚል ቢሆንም እውነታው ግን ረሃቡም
ሆነ ረሃቡን ተከትሎ የመጣው ወረርሽኝ የብልጽግና
ፖሊሲ ውጤት ነው። ሰብዓዊ ቀውሱ አድማሱን
እንዲያሰፋ የተፈለገውም ሕዝቡ የፋኖ ደጀን ነው
በሚል ሥርዓት ወለድ ጥላቻ እንደሆነ እናምናለን።
እነዚህ አካባቢዎች ዝናብ አጠር የሆኑ አካባቢዎች
ቢሆኑም ለዚህ መሰል የከፋ ችግር አልፎም የረሃብ
ተጋላጭነትን የሚያሰፋ ሰብዓዊ ቀውስ ደርሶባቸው
አያውቅም ነበር። የአሁኑ ሰብዓዊ ቀውስ የብልጽግና
አገዛዝ በአማራ ሕዝብ ላይ የያዘው ፀረ-አማራነት
ፖለቲካዊ አቋም ውጤት ነው።
በዚህም የብልጽግና አገዛዝ ረሃብን የጦር መሳሪያ
አድርጎ በመጠቀሙ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ዜጎች
በረሃብ የተነሳ ሕይወታቸው እያለፈ ይገኛል።
አሁን ለረሃብ የተጋለጡት አካባቢዎች ሰፊ የእንስሳት
ሃብት ያለባቸው እና ነዋሪዎችም በከፊል አርብቶ አደር በመሆናቸው የዛሬና የነገ ተስፋዎቻቸው የሆኑት የቤት እንስሳቶች እየረገፉ ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ የሰሜን ጎንደር ዞን አዋሳኝ የሆነው
ዋግ ኽምራ ዞንም የብልጽግና ፖሊሲ ውጤት የሆነ
ድርቅ ተከስቶ ዜጎች በረሃብ እየሞቱ፤ የአርሶ አደሮች
የቀንድና የጋማ ከብቶች እያለቁ ነው። በሰሃላ ሰየምት፣ ዝቋላ፣ አበርገሌ፣ ደሃና፣ … ወረዳዎችም ድርቁ አድማሱን አስፍቷል። አሳሳቢው ነገር ድርቁ ወደ ረሃብ ማደጉ ሲሆን፤ አገዛዙም ረሃብን የጦርነት ማሸነፊያ መሳሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት ይገኛል።
እነዚህ አካባቢዎች ቀደም ሲል በሰሜኑ ጦርነት ተጎጅ
እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት እጅግ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
በአጠቃላይ በተከዜ ተፋሰስ ስር በሚገኙ አካባቢዎች
ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች የብልጽግና አገዛዝ አማራን የማጥፋት ፖሊሲ አካል በሆነው በዕለት ደራሽ ምግብ ዜጎችን መቅጣት (ረሃብን የጦርነት ማሸነፊያ መሳሪያ ማድረግ) ፖሊሲው ሚሊዮኖች የዕለት ሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተገደዋል።
በዚህም ምክንያት ሕፃናትና ወላድ እናቶች በረሃብ
ሕይወታቸው እያለፈ ይገኛል። ስለሆነም ዓለማቀፍ የረድዔት ድርጅቶች በአማራ ግዛት በተለይም ችግሩ በከፋባቸው አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የዕለት ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርጉ ፋኖ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያረጋግጣል።
በመሆኑም፦
1) የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኤስኤአይዲን
የመሳሰሉ የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች የብልጽግና
አገዛዝ ረሃብን የጦርነት ማሸነፊያ ስልት በማድረግ
ዜጎችን ወደሞት ጎዳና እየነዳ መሆኑን አውቃችሁ
የተቋረጠውን ድጋፋችሁን በፍጥነት እንድትጀምሩ
በሕዝባችን ስም እንጠይቃለን።
2) ፋኖ፣ የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶቹ ለሥራቸው
አመችነት በተለይም ለሰራተኞቻቸው ደህንነት
አስፈላጊውን ሁሉ ጥበቃና ጥንቃቄ እንደሚያደርግ
ያረጋግጣል። በተለይም አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ
በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች በፋኖ በኩል ምንም
ዓይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደማያደርግ ይልቁንም ለዚሁ ሰብዓዊ እርዳታ ዓላማ ጥበቃ እንደሚሰጥ ያረጋግጣል።
3) በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል በተጠቀሱ
አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ፣ ወደረሃብ ያደገው
አገዛዙ ረሃብን እንደጦር መሳሪያ በመጠቀሙ ነው።
ይህ ሁኔታ አድማሱን አስፍቶ በመላ አማራ ክልል
ብሎም በመላ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ቀውሶችን አሁን
ካለንበት በከፋ መልኩ ከማባባሱ በፊት የዓለማቀፉ
ማኀበረሰብ በብልጽግና አገዛዝ ላይ ጫና እንዲያሳድር እየጠየቅን የድርቁን ሁኔታ በተመለከተ በአገዛዙ በኩል የሚቀርቡ ሐሰተኛ መረጃዎችን ውድቅ በማድረግ እውነታውን በባለሙያዎቻችሁ በኩል መሬት ወርዳችሁ እንድታረጋግጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
4) በአገር ውስጥ የምትገኙ አገር በቀል የእርዳታ
ድርጅቶችና በጎ ፍቃደኛ የሆናችሁ ግለሰቦችና ቡድኖች ለሰብዓዊ እርዳታው የምታደርጉትን ጥረት ፋኖ እያደነቀ፣ የብልጽግና አገዛዝ ረሃብን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ስለመሆኑ በተጨባጭ ማስረጃዎች እንድታጋልጡ ጥሪውን ያቀርባል።
***
ረሃብን የጦር መሳሪያ በማድረግ የሚቀለበስ የአማራ
ትግል የለም!!
የቴዎድሮስ ብርጌድ እና የሰሜን አማራ ፋኖ
መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም